በወንጀል የተከሰሰ ሰው አዲስ የወንጀል ህግ ከመውጣቱ በፊት በተፈፀመ ወንጀል ከተፈረደበት እና ሆኖም ግን ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ ስራ ላይ ከነበረው ወንጀል ህግ ይልቅ አዲሱ ህግ ለተከሳሹ ቅጣትን የሚያቀልለትና ተከሳሹን የሚጠቅም ሆኖ ከተገኘ ይሄው በአዲሱ ህግ ላይ ያለው ቅጣት የሚፈጸምበት ስለመሆኑ ከወንጀል ህጉ ቁ. 6 ድንጋጌ ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 95438 ቅጽ 6፣[1] ወ/ህ/ቁ. 6
በአንድ ወንጀል ተመሳሳይ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ተከሳሾች መካከል አንደኛው ባቀረበው የሰበር አቤቱታ መነሻነት ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ፍርድ ከተሰጠ ፍርዱ የሰበር አቤቱታ ላልጠየቁት ሆነ ጠይቀው አቤቱታቸው በአጣሪ ችሎት አያስቀርብም ተብሎ ውድቅ ለተደረገባቸው ሌሎች ተከሳሾችም ጭምር ተፈጻሚነት አለው፡፡
በተመሣሣይ የወንጀል ህግ ድንጋጌ ጥፋተኛ ተብለውና በወንጀሉ የነበራቸው ተሣትፍ እና ሌሎች ግላዊ ሁኔታዎች ተመሣሣይ ሆኖ በመገኘቱ ተመሣሣይ የሆነ የቅጣት ውሣኔ የተላለፈባቸው ሰዎች፣ የአንደኛው የሰበር አቤቱታ የሚጣራ የህግ ነጥብ ያለው መሆኑ ተገልጾ ለሰበር ችሎት ሰለቀረበና በውሣኔው ላይ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት መሆኑ ተገልጾ በሚሰጠው ፍርድ ተጠቃሚ የሚሆንበት የሌላኛው የሰበር አቤቱታ የሰበር አጣሪ ችሎት ለሰበር አያስቀርብም ተብሎ ውድቅ ስለተደረገበት ብቻ የፍርዱ ተጠቃሚ የማይሆንበትን አግባብ መከተል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 25 እና በወንጀል ህጉ አንቀጽ 4 የተደነገገውን የእኩልነት መርህ የሚጥስና የሰበርን መሠረታዊ ዓላማ የማያሳካ ይሆናል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት አንቀጽ 196 “የተፈረደባቸው ሰዎች ብዙ ሆነው አንድ ብቻ ይግባኝ ሲያቀርብ” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ 1 ቃል በቃል ሲነበብ “ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ያቀረበው ይግባኝ ስለተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች የሚመለከት ሆኖ ይግባኝ ያለው ግን የተፈረደበት አንድ ሰው ብቻ በሆነ ጊዜ ከዚህ በታች የተመለከተው ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሚሰጠው ፍርድ ይግባኝ ያላሉትም ሰዎች ይግባኝ እንዳሉ ተቆጥሮ ይፈጸምላቸዋል ለማለት የሚቻለው፤ /ሀ/ በይግባኝ የተሰጠው ፍርድ ይግባኝ ባዩን የሚጠቅም በሆነ ጊዜና /ለ/ ተከሳሾች ይግባኝ ቢሉ ኖሮ በፍርድ እነርሱም ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር የሚያሰኝ ሆኖ ሲገኝ ነው” የሚል ይሁንታ ያለው ነው፡፡
ይህንን ድንጋጌ አሁን ላለው የሰበር ስርዓት ለመጠቀም ካለው የሰበር ችሎት አደራጃጀትና አሰራር ጋር በሚጣጣምና የሰበርን መሰረታዊ ዓላማ ሊያሳካ በሚችል መንገድ መተርጎምና ስራ ላይ ማዋል ይጠይቃል፡፡ ብዙ ተከሳሾች በአንድ ወንጀል የወንጀል ስራው ተካፋይና ግብረ አበር ሆነዋል ተብለው ክስ ቀርቦባቸውና፣ ጉዳዩን በመጀመሪያ ባየው ፍርድ ቤት እና በይግባኝ ባየው ፍርድ ቤት ወይም ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት አንደኛው ተከሳሽ የሰበር አቤቱታ አቅርቦ፣ አቤቱታው ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ተብሎ በሰበር ችሎት ታይቶ፣ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ወይም በይግባኝ አይቶ ውሳኔ የሰጠው ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ወይም የቅጣት ውሳኔ ወይም የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔው መሰረታዊ ህግ ስህተት አለበት ተብሎ ከተሻረ፣ ከተሻሻለ ወይም ከተለወጠና የሰበር ችሎት በመሻር፣ በማሻሻል ወይም በመለወጥ የሰጠው ውሳኔ የሰበር አቤቱታ ያላቀረቡትን ሌሎች በአንድ ጉዳይ የተከሰሱ ሰዎችን የሚጠቅም ሆኖ በተገኘ ጊዜ፣ ሰዎቹ ፍርዱን በመቃወም የሰበር አቤቱታ ባያቀርቡም ሰበር ችሎት በሰጠው ውሳኔ ወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 196 ንዐስ አንቀጽ 1 መሰረት ተጠቃሚ እንደሆኑ በሚያደርግ አግባብ ድንጋጌው መተርጎምና ስራ ላይ መዋል አለበት፡፡
በአንድ ወንጀል አድራጎት በወንጀል ህግ ስለወንጀል ተካፋይነት አድራጊነት ወይም ስለግብረአበርነት በተደነገጉት መሰረት በአንድ ላይ ፈጽመዋል ተብለው ክስ ከቀረበባቸው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ባየውና በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ሰዎች ብዙ ሰዎች ሁሉም በግላቸው የሰበር አቤቱታ አቅርበው የሰበር መዝገብ አስከፍተው ከፊሎቹ ያቀረቡት የሰበር አቤቱታና ያስከፈቱት የሰበር መዝገብ በሰበር ችሎት የሚቀርብ መሠረታዊ የህግ ስህተት ጭብጥ የለውም ተብሎ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 22 መሠረት በሰበር አጣሪ ችሎት ውድቅ ቢደረግና ቢዘጋ የከፊሎቹ ወይም አንደኛው ተከሳሽ ያቀረበው የሰበር አቤቱታ በሰበር የሚጣራ መሠረታዊ የህግ ጭብጥ አለው ተብሎ ለሰበር ችሎት ቀርቦ የሰበር ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የጥፋተኝነት ውሣኔውን ወይም የቅጣት ውሳኔውን ወይም የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሣኔውን መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት የሰበር ችሎት ከሻረው፣ ካሻሻለው ወይም ከለወጠውና ውሳኔው የሰበር አቤቱታ አቅርበው የሰበር ማጣሪያ ችሎት የሚጣራ መሠረታዊ የህግ ስህተት ጭብጥ የለውም ብሎ አቤቱታውን ውድቅ ያደረገባቸውን ሰዎች የሚጠቅም ሆኖ በተገኘ ጊዜ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ህግ ቁጥር 196 ንዐስ አንቀፅ 1 ድንጋጌ ተፈፃሚ መሆን ይገባዋል፡፡
ሰ/መ/ቁ. 101056 ቅጽ 18፣[2] ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 25፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 196
በመርህ ደረጃ የተሻረ ሕግ ተፈፃሚነት የሌለው ሲሆን በተሻረ ሕግ ክስ ማቅረብ ደግሞ የመርሁ ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ የተሻረውም ሕግ ተጠቅሶ በተከሳሹ ላይ ክስ የሚቀርበው ወንጀሉ ተሰርቷል በተባለ ጊዜ ሕጉ ሥራ ላይ ስለነበርና ተከሣሹም ያውቀዋል ተብሎ ስለሚገመትና በሚያውቀው ሕግ መሠረት መከራከር እንዳለበት የሕግ መርህ /Rule of legality/ ስለሚያስገድድ ነው፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው የተሻረው ሕግ የሚጠቀሰው ተከሳሹ ክርክሩን በአግባቡ ለመምራት እንዲያስችለው እንጂ ከዚህ ያለፈ ውጤት የሌለውና መጨረሻም ላይ ቅጣት የሚወሰነው ሥራ ላይ ባለ ሕግ ተመስርቶ መሆኑን ነው፡፡
የዋስትና ጉዳይ በዋናነት የሚታየው ቅጣትን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ተከሳሽ የተከሰሰው የዋስትና መብት በሚከለክል ድንጋጌ ቢሆንም ድንጋጌው የሚጠቀሰው ክርክሩን በአግባቡ ለመምራት ታስቦ እንደሆነ ሕጉ ይዞት የተነሳውን ዓላማ መገንዘብ ከተቻለ የዋስትናው ጉዳይ መታየት የሚገባው ሊወሰንበት ከሚችለው ቅጣት አኳያ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ ክርክሩ እልባት ካገኘ በኋላ ተከሳሹ የሚቀጣው በአዲሱ ሕግ መሠረት እንደሆነ ከወዲሁ በግልጽ መገንዘብ ከተቻለ ክርክሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በእሥር ይቆይ ማለት ሕግ አውጭው የዋስትና መብት ሊከለክላቸው ያልፈለገውን ተከሣሾች የዋስትና መብት እንደመከልከል የሚቆጠርና ሕጉም የታለመለትን ዓላማና ግብ እንዳይመታ የሚያደርግ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 34077 ቅጽ 7[3]
[1] አመልካች አቶ ሰለሞን ደሣለኝ እና ተጠሪ የደቡብ ክልል ዐ/ህግ ግንቦት 07 ቀን 2006 ዓ.ም.
[2] አመልካች አቶ አይሸሽም ገብሬ እና ተጠሪ የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.
[3] አመልካች አቶ ሰይድ ይመር እና ተጠሪ የአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም.
Filed under: Articles, Case Comment
